Articles, World News

የ2012 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ ይካሄድ ወይስ ይራዘም? – ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር)

ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ፖለቲካውን አረጋግተን፣ የለውጥ ኀይሉ ተጠናክሮ፣ ቀልባሾቹ ሽንፈታቸውን በፀጋ ተቀብለው ወይም በንሰሃ ወደለውጡ መንገድ ተመልሰው ከዚያ በኋላ ምርጫ አዘጋጅተን የተለመደው ዓይነት ሳይሆን ዶ/ር ዐቢይ እንዳለው በሕዝብም በመንግሥትም በተፎካካሪ ፓርቲዎችም በሚታዘቡ ወዳጅ አገሮችም ተዓማኒ የሆነ ምርጫ ማካሄድ እንችላለን ወይ? ነው ጥያቄው፡፡ በእኔ አስተያየት ፍፁም የማይሆን ተስፋ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ተዓማኒ የሆነ ምርጫ ማድረግ በምንችልበት ሁኔታ ውስጥ አይደለንም፡፡

ገና ቀጣይ ቅልበሳዎችና ቀጣይ ቀውሶች አይኖሩም ብለን እንኳን ማረፍ አንችልም፡፡ የዲሞክራሲያዊ ምኅዳሩን አደላድለን፣ ፍፁም ባይሆንም ሊያሠሩ የሚችሉ ተቋማትን አዘጋጅተን፣ ተዓማኒነት ያለው መርጫ ማካሄድ እንችላለን የሚለውን አጀንዳ ማንሳት ቀርቶ ይህ ለውጥ በማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለን ማውራትስ እንችላለን ወይ? ይህንን ዓመትም ማውራት ምንችል መሆናችንን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ስለዚህ 2012 ዓመተ ምሕረትን እንደማይገፋ የቃል ኪዳን መስመር መቁጠር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ መሠረታዊ ነጥብ ምርጫ መቼ ይካሄዳል የሚለው መሆን የለበትም፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት እኮ በምርጫ ስም ተለያዩ አስቀያሚ ድራማዎችን ስናይ የኖርን፣ ወደ መጨረሻ አካባቢ 99.6 እና በኋላ በመቶ በመቶ አሸነፍሁ የሚለውን ቀልድ ካየን በኋላ ምርጫ የሚለውን ተውኔት ዘግተናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ቲያትር የማየት ፍላጎት ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፡፡ ቲያትር ማየትም ካለብን እውነተኛ ፖለቲካ ትግል የሚታይበት፣ በደንብ ተሠራ ፖለቲካዊ ጨዋታ ነው ማየት የምንፈልገው፡፡

ምርጫ ማድረግ አይቻልም ብሎ መዝጋት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ምክንያም ፀረ-ለውጥ ኀይሉ እያንዳንዷን አጀንዳ እየመዘዘ ማሳጣትና ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት መሥራቱ አይቀርምና ነው፡፡ “ይኸው ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌላ መሠረት እንዳይካሄድ ተደረገ፤ አምባገነንነት ሰፈነ፤” ወዘተ. የሚል ነጠላ ዜማ ሊለቀቅ ይችላል፡፡ ስለሆነም በመርህ ደረጃ ምርጫውን በ2012 ዓ.ም. ማካሄድ ምንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ምርጫውን ማካሄድ እንደተለመደው አንድ የተለመደ ዝግጅት ማካሄድ ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሒደቱን እንየው፡፡

በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለጻና ገለልተኛ ተቋማትን ገንብተን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እረፍትና ፋታ አግኝተዋል ብለን ካመንን ምርጫውን በ2012 ዓ.ም. ማድረግ እንችላለን፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ምርጫን ለማካሄድ ብለን በተለመደው ዓይነት የቀልድና የፌዝ መንገድ መሄድ የለብንም፡፡ የለውጥ ኀይሉም እንዲህ ዓይነት ቲያትር የመጫወትና የነቀፈው ወራዳ ተግባር ውስጥ የመግባት ፍላጎት ያለው አይመስለኝም፡፡ ቁምነገሩ በቀልደኛው ሕገ መንግሥት የተቆረጠው 2012 የሚለው የጊዜ ሰሌዳ መከበር አለመከበሩ ሳይሆን መሠረታዊ የሆኑ ቅድመ-ሁኔታዎችን ያሟላ፣ እንደተባለውም በሕዝቡ፣ በመንግሥት፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎችና በታዛቢዎች ዘንድ ተዓማኒ የሆነ ምርጫ ማካሄድ የምንችልበት ጊዜ መቼ ነው? የሚለው ነው፡፡ የጊዜ ሰሌዳን ለማክበር ሲባል ብቻ የመጀመሪያውን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የማካሄድ ወርቃማ ዕድላችንን ማክሸፍ የለብንም፡፡ እንዲያ ከሆነ አደገኛ ቁማር መበላት ነው የሚሆነው፡፡

የትኩረታችን አቅጣጫ የጊዜ ሰሌዳውን የመጠበቅ ያለመጠበቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከ2012 ዓ.ም. በኋላ ዶ/ር ዐቢይ የሚመሩት መንግሥት ሕጋዊ ሥልጣን (mandate) አይኖረውም የሚል አስተያየት እንደሚቀርብ ይገባኛል፡፡ በበኩሌ እንደዚህ ዓይነት ቀልድ አልሰማም፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ መቼም ቢሆን ሕጋዊና አግባብነት ያለው (legitimate) ሥልጣን ኖሮት አገር መርቶ አያውቅም፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የጨዋታዎችን ስሞች ቀየረ እንጂ በጠመንጃ ገብቶ በጠመንጃ ነው የኖረው፡፡ ስለዚህ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ካልተካሄደ ዲሞክራሲያችን ይደናቀፍብናል የሚል የሞኝ ክርክርና ወሬ ማውራት የለብንም፡፡ ሕዝብን ከሚያሸማቅቅ፣ ማንኛውንም መንግሥታዊና ኅብረተሰባዊ ተቋማትን ጠርንፎ ይዞ መቶ በመቶ ከሚያሸንፍ የጨለማ አገዛዝ ወጥተን፣ ሁላችንም ጥሩ ነው ብለን ልንቀበለው የምንችል ምርጫ ማካሄድ ካልቻልን ዋጋ የለውም፡፡

ትልቁ ችግር የለውጥ ኀይሉ አባላት አሁንም በዚያው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥቅመኞችን በያዘው ቡድን ውጥ ናቸው፡፡ ይህ የጥቅመኞች ስበስብ ደግሞ እነ ዶ/ር ያገኙትን ሕዝባዊ ተቀባይነት ተጠቅመን ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣኑን ለማደላደል እንደሚፈልግና ለዚህም ሌት ተቀን ተግቶ እንደሚሠራ ጥርጥር የለውም፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ተወዳጅነቴና ተፈላጊነቴ ሳይጠወልግ ቶሎ ምርጫ እንዲካሄድ አድርጌ ሥልጣኔን አደላድዬ ከዚያ በኋላ የሚሆነውን አያለሁ የሚሉ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ዶ/ር ዐቢይ በሚመሩት ድርጅት ውስጥ የተሰገሰጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥቅመኞች ያከተመ የፖለቲካ ሥልጣናቸውን ለማራዘም የለውጥ ኀይሉን ተፈላጊነት እንደ ዕድሜ ማራዘሚያ ለመጠቀም ሌት ተቀን ከመሥራት አይመለሱም፡፡

(Visited 6 times, 1 visits today)
November 9, 2018

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: abcd@gmail.com

Logo